የወር አበባ ጊዜ ህመም ከተለመደው በላይ ሆኖ ችግርን ሲያመለክት፦ ስለ ማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) ማወቅ

የጤና መረጃዎች

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) ምንድን ነው?

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) እንዲሁም ማዮማ /Myoma ወይም ሊዮማዮማ/ Leiomyoma ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በማህፀን የጡንቻ ሽፋን ውስጥ የሚያድግ ካንሰር ያልሆነ (benign) የሕዋስ እድገት ነው።

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ በጣም የተለመዱ የማህፀን ችግሮች አንዱ ነው። አንዳንድ ሴቶች ምንም ዓይነት ምልክት ላይታይባቸው ይችላል፤ ሌሎች ግን ብዙ የወር አበባ መፍሰስ፣ የዳሌ አካባቢ ህመም ወይም የመውለድ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል።

የፋይብሮይድ ምርመራ በአጠቃላይ የታካሚዋን የሕክምና ታሪክ መገምገም፣ የአካል ምርመራ እና የአልትራሳውንድ/ Ultrasound ምርመራን ያካትታል። የሕክምና አማራጩ የፋይብሮይድ መጠን፣ ብዛት፣ ቦታ፣ የሚያመጣው ምልክት ክብደት እና የታካሚዋ የወደፊት የመውለድ እቅድ ላይ ተመስርቶ ይወሰናል። ሕክምናው ከክትትልና መድሃኒት እስከ በትንሽ ቁስል የሚደረግ ቀዶ ሕክምና ወይም ላፓሮስኮፒክ እና ሮቦቲክ ቀዶ ሕክምና ሊደርስ ይችላል።

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) እድገትን ሊያመጡ የሚችሉ ምክንያቶች

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids)መከሰትና ማደግ ከተለያዩ ምክንያቶች ጋር ይያያዛል። ከእነዚህም፦

  • ኤስትሮጅን (Estrogen) – የሴቶች የመራቢያ ሆርሞን
  • ኤስትሮጅን የያዙ መድሃኒቶች ወይም ንጥረ ነገሮች
  • የዘር ሁኔታዎች (Genetic factors) – በቤተሰብ ውስጥ የማህፀን ፋይብሮይድ የነበረ ታሪክ ካለ የመከሰት እድሉ ሊጨምር ይችላል።

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) ዓይነቶች

ፋይብሮይዶች በማህፀን ውስጥ በሚያድጉበት ቦታ መሠረት ይከፈላሉ።

1. ሰብሴሮሳል ፋይብሮይድ/ Subserosal Fibroids – በማህፀን ውጫዊ ክፍል የሚያድግ

ይህ ዓይነት ፋይብሮይድ ከማህፀን ውጫዊ ገጽ ላይ ተነስቶ ከማህፀን ግድግዳ ውጭ ወደ ዳሌ አካባቢ ይዘረጋል።

ብዙ ጊዜ ግልጽ ምልክት አያሳይም፤ ነገር ግን ትልቅ ከሆነ እንደ ፊኛ (bladder) እና አንጀት (bowel) ያሉ በአቅራቢያው ያሉ አካላትን በመጫን ችግር ሊያመጣ ይችላል።

2. ኢንትራሚውራል ፋይብሮይድ/ Intramural Fibroids – በማህፀን የጡንቻ ግድግዳ ውስጥ የሚያድግ

ይህ የፋይብሮይድ ዓይነት በማህፀን የጡንቻ ግድግዳ ውስጥ የሚያድግ ሲሆን በብዛት የሚገኘው ዓይነት ነው።

ሊያመጣቸው ከሚችሉት ምልክቶች፦

  • ብዙ ወይም ለረጅም ጊዜ የሚፈስ የወር አበባ
  • በወር አበባ ጊዜ ከባድ ህመም
  • የመፀነስ ችግር

3. ሰብሚውኮሳል ፋይብሮይድ/ Submucosal Fibroids – ከማህፀን ውስጣዊ ሽፋን ስር የሚያድግ

ይህ ዓይነት ፋይብሮይድ ከማህፀን ውስጣዊ ሽፋን ስር የሚያድግ ሲሆን ወደ ማህፀን ውስጣዊ ክፍተት ሊገፋ ይችላል።

በመጠኑ ትንሽ ቢሆንም እንኳ ያልተለመደ የማህፀን ደም መፍሰስ እና ከመፀነስ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሊያመጣ ይችላል።

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids)  የተለመዱ ምልክቶች

ምልክቶቹ በፋይብሮይዱ መጠን፣ ብዛት እና ቦታ ላይ ይመሰረታሉ። የተለመዱት ምልክቶች፦

  • ብዙ፣ ረዥም ጊዜ የሚቆይ ወይም በተደጋጋሚ የሚመጣ የወር አበባ፤ ይህም የደም ማነስን (Anemia) ሊያስከትል ይችላል
  • በዳሌ አካባቢ ህመም ወይም ጫና
  • በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት ከባድ ቁርጠት/ህመም
  • በተደጋጋሚ መሽናት ወይም ፊኛን ሙሉ በሙሉ ባዶ ማድረግ መቸገር
  • ፋይብሮይዱ በአንጀት ላይ በሚያደርገው ጫና ምክንያት የሆድ ድርቀት
  • በዳሌ ወይም በሆድ አካባቢ የሚሰማ ወይም የሚታይ ጉብታ/እብጠት
  • ለመፀነስ መቸገር ወይም ተደጋጋሚ የፅንስ መጨንገፍ

ነገር ግን ብዙ ሴቶች ምንም ምልክት ሳይኖራቸው የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids)ሊኖራቸው ይችላል። በመደበኛ የማህፀን ምርመራ ወይም አልትራሳውንድ/Ultrasound በአጋጣሚ ሊገኝ ይችላል።

ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች

  • የፋይብሮይድ መጠምዘዝ (Torsion): በትንሽ ግንድ ላይ የተጣበቀ ፋይብሮይድ ከተጠለወ ድንገተኛና ከባድ ህመም ሊያመጣ ይችላል
  • የሽንት ቱቦ (ureter) መጨናነቅ: ፋይብሮይዱ የሽንት ቱቦን (ureter) ከተጫነ የኩላሊት እብጠት (Hydronephrosis) ሊያስከትል ይችላል።
  • የፋይብሮይድ መበላሸት (Fibroid degeneration): ፋይብሮይዱ ከሚያገኘው የደም አቅርቦት በላይ ሲያድግ የፋይብሮይድ ክፍል ሊበላሽ ይችላል፤ ይህም በተለይ በእርግዝና ጊዜ ከባድ ህመም ሊያመጣ ይችላል።
  • ፋይብሮይድ ወደ ካንሰር የመቀየር እድሉ በጣም ዝቅተኛ ሲሆን ከ1% በታች ነው።

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) እንዴት ይመረመራል?

ምርመራው ሊያካትት የሚችለው፦

  • የሕክምና ታሪክ እና የአካል ምርመራ
  • የዳሌ/የማህፀን አካባቢ ምርመራ (Pelvic examination)
  • የዳሌ አካባቢ አልትራሳውንድ/ Ultrasound

ትክክለኛ ምርመራ ለእያንዳንዱ ታካሚ ተስማሚ የሕክምና ዕቅድ ለመወሰን አስፈላጊ ነው።

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) የሕክምና አማራጮች

የሕክምና አማራጩ በምልክቶቹ፣ በፋይብሮይዱ መጠንና ቦታ እንዲሁም ታካሚዋ ወደፊት ልጅ ለመውለድ ያላት እቅድ ላይ ይመሰረታል።

1. ክትትል እና መደበኛ ምርመራ

ፋይብሮይዱ ትንሽ ከሆነ፣ ምልክቶቹ ቀላል ከሆኑ እና ምንም ችግር ካልተከሰተ በመደበኛ ምርመራ እና አልትራሳውንድ/ Ultrasound እየተከታተሉ መቆየት ሊመከር ይችላል።

2. መድሃኒት

በአሁኑ ጊዜ የማህፀን ፋይብሮይድን (Uterine Fibroids) ሙሉ በሙሉ በቋሚነት የሚያስወግድ መድሃኒት የለም። ሆኖም መድሃኒቶች ህመምን ለመቀነስ እና ከፍተኛ የወር አበባ ደም መፍሰስን ለመቆጣጠር ሊረዱ ይችላሉ።

3. ቀዶ ሕክምና

ቀዶ ሕክምና የፋይብሮይድን ማስወገድ (ማዮሜክቶሚ/ Myomectomy) ወይም ማህፀንን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ (ሂስተሬክቶሚ/ Hysterectomy) ሊያካትት ይችላል።

ላፓሮስኮፒክ ቀዶ ጥገና – Laparoscopic Surgery – በትንሽ ቁስል የሚደረግ ቀዶ ሕክምና

በሆድ ላይ በሚደረጉ በርካታ ትንንሽ ቀዳዳዎች/ ቁስሎች፣ በአብዛኛው 0.5–1 ሴ.ሜ ሲሆኑ፣ ካሜራ እና ልዩ የቀዶ ጥገና ሕክምና መሳሪያዎችን በመጠቀም የሚደረግ ሂደት ነው።

ጥቅሞቹ ሊያካትቱ የሚችሉት፦

  • አነስተኛ ጠባሳ
  • ከቀዶ ሕክምና በኋላ ያነሰ ህመም
  • ፈጣን ማገገም

ኤን.ኦ.ቲ.ኢ.ኤስ / ናቹራል ኦሪፊስ ትራንስሉሚናል ኢንዶስኮፒክ ቀዶ ጥገና – NOTES (Natural Orifice Transluminal Endoscopic Surgery)

ኤን.ኦ.ቲ.ኢ.ኤስ /NOTES የሆድ ላይ ቁስል ሳይደረግ በተፈጥሯዊ የሰውነት ክፍተት ለምሳሌ የሴት ብልትን በመጠቀም የሚደረግ ጠባሳ የማይታይበት የቀዶ ሕክምና ዘዴ ነው።

ታካሚዎች ከቀዶ ሕክምና በኋላ ያነሰ ህመም ሊሰማቸው እና በሆድ ላይ የሚታይ ጠባሳ ላይኖር ይችላል። ይህ ዘዴ በተመረጡ ታካሚዎች ላይ ማህፀንን ለማስወገድ (ሂስተሬክቶሚ/Hysterectomy) ሊጠቅም ይችላል።

ዳ ቪንቺ ሮቦቲክ የቀዶ ሕክምና ዘዴ – Da Vinci Robotic-Assisted Surgery

ዳ ቪንቺ ሮቦቲክ የቀዶ ሕክምና/ Da Vinci Robotic Surgery የላፓሮስኮፒክ/ Laparoscopic ቀዶ ሕክምናን ከሮቦቲክ ቴክኖሎጂ ጋር የሚያጣምር ዘመናዊ ቀዶ ሕክምና ዘዴ ነው።

ዶክተሩ ቀዶ ሕክምናውን በኮንሶል ላይ ተቀምጦ በከፍተኛ ጥራት ያለው 3-ዲ/ 3D ምስል በመመልከት ይቆጣጠራል። ይህም በቀዶ ሕክምናው ወቅት የበለጠ ትክክለኛና የተሻሻለ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ያግዛል።

ሆኖም የዳ ቪንቺ/ Da Vinci ሮቦቲክ ሲስተም ለታካሚው ተስማሚ መሆኑን የሚወስነው ዶክተሩ በታካሚው የጤና ሁኔታ እና የሕክምና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ነው።

ስለ ማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) ካንሰር ነው?

በአብዛኛው የማህፀን ፋይብሮይድ ካንሰር ያልሆነ (benign) የሕዋስ እድገት ነው። ወደ ካንሰር የመቀየር እድሉ በጣም ዝቅተኛ ሲሆን ከ1% በታች ነው።

ምልክት ከሌለ የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) ሕክምና ያስፈልገዋል?

ወዲያውኑ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አያስፈልግም። ሁኔታውን በመደበኛ ምርመራ መከታተል እና የፋይብሮይዱን መጠን በጊዜ ሂደት መመርመር ይቻላል።

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) የመውለድ ችሎታን ሊጎዳ ይችላል?

በአንዳንድ ሁኔታዎች በተለይም ፋይብሮይዱ በማህፀን ውስጣዊ ክፍተት ውስጥ ከሆነ መፀነስ እንዳይቻል ወይም የፅንስ መጨንገፍ እንዲከሰት አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል።

የማህፀን ፋይብሮይድ (Uterine Fibroids) ላለባቸው ሁሉም ታካሚዎች ቀዶ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል?

አይ፤ ቀዶ ሕክምና ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም የሚለው ውሳኔ በምልክቶቹ ክብደት፣ በፋይብሮይዶቹ መጠንና የእድገት ፍጥነት እንዲሁም በተከሰቱ ችግሮች ላይ ይመሰረታል።

ዳ ቪንቺ ሮቦቲክ የቀዶ ሕክምና ዘዴ/ Da Vinci Robotic Surgery ለማን ሊመከር ይችላል?

ዳ ቪንቺ ሮቦቲክ የቀዶ ሕክምና ዘዴ/ Da Vinci Robotic Surgery በትንሽ ቁስል ቀዶ ሕክምና ሊታከሙ ለሚገባቸው ታካሚዎች አንዱ የሕክምና አማራጭ ሊሆን ይችላል።

ለታካሚው ተስማሚ መሆኑ ግን በትክክለኛ የሕክምና ምርመራ እና በማህፀን ስፔሻሊስት ግምገማ መሠረት መወሰን አለበት።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እባክዎን ያነጋግሩን

የሴቶች የጤና ማዕከል ፤ ቬጅታኒ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል

ስልክ፦ (+66) 2-734-0000 Ext. 3200, 3204

የአማርኛ ስልክ መስመር: (+66) 90-907-2560

Readers’ Rating

0.0 out of 5 stars (based on 0 reviews)