የዳሌ መገጣጠሚያ አጥንት የደም አቅርቦት መቋረጥ — ኤ.ቪ.ኤን (Avascular Necrosis of the Hip — AVN) በዳሌ አጥንት ክፍል ውስጥ የደም አቅርቦት ሲቀንስ ወይም ሲቋረጥ የሚከሰት ችግር ነው። በጊዜ ሂደት የተጎዳው አጥንት ደካማ ሊሆንና ሊፈርስ ይችላል።
ይህ በሽታ ብዙውን ጊዜ በጭን አጥንት የላይኛው ክብ ክፍል (Femoral Head) ላይ ይከሰታል። ይህ ክፍል የዳሌ መገጣጠሚያን የሚፈጥረው የኳስ ቅርጽ ያለው ክፍል ነው። በሽታው የዳሌ አጥንት ኔክሮሲስ (Osteonecrosis of the Hip) ተብሎም ይጠራል።
በመጀመሪያ ደረጃ አንዳንድ ሰዎች ምንም ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። ምልክቶች ሲጀምሩ ግን በዳሌ፣ በብሽሽት አካባቢ ወይም በጭን የላይኛው ክፍል ላይ ህመም ሊሰማ ይችላል። መጀመሪያ ላይ ህመሙ በእግር ሲሄዱ ወይም በተጎዳው እግር ላይ ክብደት ሲያሳርፉ ሊታይ ይችላል። በጊዜ ሂደት ህመሙ እየባሰ ሊሄድና መራመድን ወይም ደረጃ መውጣትን የመሳሰሉ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ሊገድብ ይችላል።
ሕክምና ካልተደረገለት የአጥንቱ መጎዳት እየተባባሰ ሊሄድ፣ የጭን አጥንቱ ክብ ቅርጽ ሊቀየርና የዳሌ መገጣጠሚያው ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። በመጨረሻም የመገጣጠሚያ አርትራይተስ (Arthritis) ሊከሰት ይችላል።
የሕክምና አማራጮች በበሽታው ደረጃ ላይ ይመሰረታሉ። የዳሌ መገጣጠሚያው ከባድ ጉዳት ከመድረሱ በፊት በሽታውን ማወቅ የተለያዩ የሕክምና አማራጮችን ሊያበረክት ይችላል።
የዳሌ መገጣጠሚያ አጥንት የደም አቅርቦት መቋረጥ — ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ምንድን ነው?
የዳሌ መገጣጠሚያ ኳስና መቀበያ ቅርጽ (Ball-and-Socket Joint) አለው። በጭን አጥንት ላይ የሚገኘው ክብ ክፍል ኳሱን ሲፈጥር በዳሌ አጥንት ውስጥ ያለው መቀበያ ክፍል ደግሞ ኳሱን ይይዛል።
አጥንት ሕያው ሕብረ ሕዋስ ስለሆነ ጤናማ ሆኖ ለመቆየት ዘላቂ የደም አቅርቦት ያስፈልገዋል። ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ሲከሰት ወደ ጭን አጥንት የላይኛው ክብ ክፍል የሚደርሰው የደም ፍሰት ይቀንሳል ወይም ይቋረጣል። በዚህም የተጎዳው አጥንት ቀስ በቀስ ጥንካሬውን ያጣና ሊጎዳ ይችላል።
እነዚህ ለውጦች ሁልጊዜ ወዲያውኑ ምልክት አያስከትሉም። በአንዳንድ ሰዎች ከባድ ህመም ከመጀመሩ በፊት በሕክምና ምርመራ ሊታወቅ ይችላል። በሌሎች ሰዎች ግን በዳሌ ወይም በብሽሽት አካባቢ የሚሰማ ህመም የመጀመሪያው ግልጽ ምልክት ሊሆን ይችላል።
የዳሌ አጥንት የደም አቅርቦት መቋረጥ — ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ምልክቶች
የኤ.ቪ.ኤን (AVN) ህመም ብዙውን ጊዜ በዳሌ ወይም በብሽሽት አካባቢ ይሰማል። ህመሙ ወደ ጭን ወይም ወደ መቀመጫ አካባቢ ሊዘልቅ ይችላል። በእግር ሲሄዱ፣ ለረጅም ጊዜ ቆመው ሲቆዩ ወይም በተጎዳው እግር ላይ ክብደት ሲያሳርፉ ህመሙ ብዙውን ጊዜ ይጨምራል።
በሽታው እየጨመረ ሲሄድ ህመሙ በተደጋጋሚ ሊከሰትና በእረፍት ጊዜም ሊሰማ ይችላል። ዳሌው ሊደነድን ወይም ለማንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ይህም የዕለት ተዕለት ሥራዎችን ሊያተጓጉል ይችላል።
የተለመዱ ምልክቶች፦
በዳሌ ወይም በብሽሽት አካባቢ ህመም
በእግር ሲሄዱ ወይም በእግር ላይ ክብደት ሲያሳርፉ የዳሌ ህመም
ወደ ጭን ወይም ወደ መቀመጫ አካባቢ የሚዘልቅ ህመም
የዳሌ መደንደን ወይም እንቅስቃሴ መገደብ
በእግር ለመሄድ መቸገር ወይም በአንድ እግር ላይ አዘንብሎ መሄድ
በበሽታው የተራቀቁ ደረጃዎች ላይ በእረፍት ጊዜም ህመም መሰማት
ምልክቶች ከሰው ወደ ሰው ሊለያዩ ይችላሉ። በሽታው እየጨመረ ሲሄድ በእግር ሲሄዱ የሚሰማው ህመምና የዳሌ እንቅስቃሴ መገደብ ይበልጥ ግልጽ ሊሆኑ ይችላሉ።
መንስኤዎችና የአደጋ ምክንያቶች
ኤ.ቪ.ኤን (AVN) የሚከሰተው ወደ ጭን አጥንት የላይኛው ክብ ክፍል የሚደርሰው የደም አቅርቦት ሲቀንስ ወይም ሲቋረጥ ነው። ይህ በዳሌ አካባቢ ያሉ የደም ሥሮችን በሚጎዳ አደጋ ምክንያት ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን በብዙ ሁኔታዎች በሽታው ከቀጥተኛ ጉዳት ይልቅ ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ይያያዛል።
የተለመዱ የአደጋ ምክንያቶች፦
የዳሌ ጉዳት፦ የአጥንት ስብራት ወይም የመገጣጠሚያ መፈናቀል ወደ ጭን አጥንት ደም የሚያደርሱ የደም ሥሮችን ሊጎዳ ይችላል።
የኮርቲኮስቴሮይድ መድኃኒቶች አጠቃቀም (Corticosteroids) ፦ እነዚህን መድኃኒቶች ለረጅም ጊዜ መውሰድ ወይም ከፍተኛ መጠን መጠቀም የኤ.ቪ.ኤን (AVN) አደጋን ሊጨምር ይችላል።
ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት፦ ለረጅም ጊዜ ብዙ አልኮል መጠጣት ከኤ.ቪ.ኤን (AVN) አደጋ መጨመር ጋር ይያያዛል።
አንዳንድ የጤና ችግሮች፦ የደም በሽታዎችና አንዳንድ የራስ-መከላከያ ሥርዓት በሽታዎች (Autoimmune Diseases) ወደ አጥንት የሚደርሰውን የደም ፍሰት ሊያውኩ ይችላሉ።
አንዳንድ የሕክምና ሂደቶች፦ የጨረር ሕክምና (Radiation Therapy) እና የአጥንት ጤናን የሚነኩ አንዳንድ ሕክምናዎች አደጋውን ሊጨምሩ ይችላሉ።
አንዳንድ ጊዜ ግልጽ የሆነ መንስኤ ሳይገኝም ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ሊከሰት ይችላል። ምክንያቱ ሳይታወቅ ሲቀር ይህ ሁኔታ ያልታወቀ መንስኤ ያለው የአጥንት የደም አቅርቦት መቋረጥ (Idiopathic Avascular Necrosis) ይባላል።
የዳሌ አጥንት የደም አቅርቦት መቋረጥ እንዴት ይመረመራል?
ምርመራው የሚጀምረው የዳሌ ህመሙን አይነትና ከበሽታው ጋር የተያያዙ የአደጋ ምክንያቶችን በመለየት ነው። ሐኪሙ ስለ ምልክቶችዎ፣ ቀደም ሲል ስለደረሰብዎ የዳሌ ጉዳት፣ አሁን ስለሚወስዷቸው መድኃኒቶችና ስለ አጠቃላይ የጤና ሁኔታዎ ይጠይቃል። በአካላዊ ምርመራው ወቅት ዳሌውን በጥንቃቄ በማንቀሳቀስ መደንደን፣ ህመም ወይም የእንቅስቃሴ ገደብ እንዳለ ይመረምራል።
በአጥንቱ ውስጥ የሚከሰቱ ለውጦች ምልክቶቹ ከመባባሳቸው በፊት ሊጀምሩ ስለሚችሉ የምስል ምርመራዎች አስፈላጊ ናቸው።
ኤክስ-ሬ (X-ray) ፦ የዳሌ መገጣጠሚያውን ለማየት ይረዳል። በጭን አጥንት የላይኛው ክብ ክፍል ላይ የሚታዩ ለውጦችን፣ አጥንቱ መፍረስ መጀመሩን ወይም የመገጣጠሚያ ጉዳትን ሊያሳይ ይችላል። ሆኖም በመጀመሪያ ደረጃ ያለ ኤ.ቪ.ኤን (AVN) በኤክስ-ሬ ላይ ሁልጊዜ ላይታይ ይችላል።
ኤም.አር.አይ (MRI) ፦ በአጥንቱ ውስጥ ያሉ ለውጦችን በበለጠ ዝርዝር ያሳያል። በኤክስ-ሬ ላይ ላይታዩ የሚችሉ ቀደምት ለውጦችን ሊለይ ይችላል። እንዲሁም የተጎዳው አካባቢ የት እንደሚገኝና የጉዳቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ይረዳል።
የምስል ምርመራ ውጤቶች በሽታው ምን ያህል እንደጨመረ እና የጭን አጥንቱ ክብ ቅርጽ እንደጠበቀ ለመወሰን ይረዳሉ። ይህ ልዩነት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም አጥንቱ ከመፍረሱ በፊትና ከፈረሰ በኋላ የሚመከሩ ሕክምናዎች ሊለያዩ ይችላሉ።
የኤ.ቪ.ኤን (AVN) ደረጃዎች
የአጥንት የደም አቅርቦት መቋረጥ ከአጥንቱ ውስጥ በሚከሰቱ ቀደምት ለውጦች ጀምሮ እስከ የዳሌ መገጣጠሚያው ከባድ ጉዳት ድረስ ሊራመድ ይችላል። የበሽታው ደረጃ የሚወሰነው በምስል ምርመራ ውጤቶችና በጭን አጥንቱ የላይኛው ክብ ክፍል ሁኔታ ላይ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ በአጥንቱ ውስጥ ለውጦች ቢጀምሩም የጭን አጥንቱ ክብ ቅርጽ ሊጠበቅ ይችላል። እነዚህ ቀደምት ለውጦች በመደበኛ ኤክስ-ሬ ከሚታዩት ይልቅ በኤም.አር.አይ ምርመራ በቀላሉ ሊለዩ ይችላሉ።
በሽታው እየጨመረ ሲሄድ የተጎዳው አጥንት እየደከመ ይሄዳል። ከመገጣጠሚያው ወለል በታች ትንንሽ ለውጦች ሊፈጠሩና የጭን አጥንቱ ክብ ቅርጽ መጥፋት ሊጀምር ይችላል።
በተራቀቁ ደረጃዎች የጭን አጥንቱ ክብ ክፍል በከፊል ሊፈርስ ይችላል። ይህ ሲከሰት ለስላሳ መሆን ያለበት የመገጣጠሚያው ወለል ያልተስተካከለ ይሆናል፤ በጊዜ ሂደትም አርትራይተስ ሊከሰት ይችላል።
የኤ.ቪ.ኤን (AVN) ደረጃ ለሕክምና ዕቅድ አስፈላጊ ነው። ተፈጥሯዊውን የዳሌ መገጣጠሚያ ለማዳን የሚያግዙ ሕክምናዎች ብዙውን ጊዜ አጥንቱ ከመፍረሱ በፊት ይታሰባሉ። የመገጣጠሚያው ጉዳት ከባድ ከሆነ ግን የተለየ የሕክምና አቀራረብ ሊያስፈልግ ይችላል።
ለኤ.ቪ.ኤን (AVN) የሚደረጉ ሕክምናዎች
ሕክምናው የሚወሰነው በበሽታው ደረጃ፣ በተጎዳው አጥንት መጠን፣ በህመሙ ክብደትና የጭን አጥንቱ መፍረስ መጀመሩ ወይም አለመጀመሩ ላይ ነው። ሐኪሙ የታካሚውን ዕድሜ፣ አጠቃላይ የጤና ሁኔታና የዳሌ መገጣጠሚያውን ሁኔታም ያገናዝባል።
በመጀመሪያ ደረጃ የሚደረግ ሕክምና
የጭን አጥንቱ ክብ ክፍል ገና ካልፈረሰ ሕክምናው ህመሙን ለማስታገስና በተጎዳው ዳሌ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ሊያተኩር ይችላል። እንደ ግለሰቡ ሁኔታ የሚከተሉት ሊመከሩ ይችላሉ፦
መድኃኒቶች፦ ህመምን ለማስታገስ ወይም እብጠትን ለመቀነስ የሚያገለግሉ መድኃኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ።
በዳሌ ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ፦ እንደ መሮጥ፣ መዝለል ወይም ለረጅም ጊዜ መራመድ ያሉ በዳሌ ላይ ተደጋጋሚ ጫና የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን መገደብ ሊያስፈልግ ይችላል።
የመራመጃ ድጋፍ፦ በተጎዳው ዳሌ ላይ የሚደርሰውን ክብደት ለመቀነስ ለተወሰነ ጊዜ ክራንች (Crutches) ወይም ሌሎች የመራመጃ መርጃዎች ሊመከሩ ይችላሉ።
የአካል ሕክምና (Physical Therapy) ፦ የዳሌ እንቅስቃሴን ለመጠበቅና በመገጣጠሚያው ዙሪያ ያሉ ጡንቻዎችን ለማጠናከር የተመረጡ ልምምዶች ሊረዱ ይችላሉ።
በአንዳንድ ታካሚዎች የጭን አጥንቱ ከመፍረሱ በፊት ተፈጥሯዊውን አጥንት ለመጠበቅ ቀዶ ጥገና ሊታሰብ ይችላል። ከእነዚህ አንዱ የአጥንት ውስጣዊ ጫናን የመቀነስ ሂደት (Core Decompression) ነው። በዚህ ሂደት በተጎዳው አካባቢ ከአጥንቱ ውስጥ ትንሽ ክፍል በማስወገድ ጫናውን ለመቀነስና በአጥንቱ ውስጥ የደም ፍሰትን ለመደገፍ ይሞከራል። እንደ አጥንቱ ጉዳት መጠን ከዚህ ሂደት ጋር ሌሎች የቀዶ ጥገና ዘዴዎችም ሊጣመሩ ይችላሉ።
በተራቀቀ ደረጃ ላይ የሚደረግ ሕክምና
የጭን አጥንቱ ክብ ክፍል ከፈረሰ ወይም የዳሌ መገጣጠሚያው ከባድ ጉዳት ካጋጠመው ተፈጥሯዊውን መገጣጠሚያ ለማዳን የሚደረጉ ሕክምናዎች ተስማሚ ላይሆኑ ይችላሉ።
ህመሙና የመገጣጠሚያ ጉዳቱ መራመድን፣ እንቅስቃሴን ወይም የዕለት ተዕለት ሥራዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ሲያስቸግሩ የዳሌ መገጣጠሚያ ሙሉ ምትክ ቀዶ ጥገና (Total Hip Replacement) ሊታሰብ ይችላል። በዚህ ቀዶ ጥገና የተጎዱት የመገጣጠሚያ ክፍሎች ይወገዳሉ፤ ከዚያም በምትክ የሚገጠሙ ሰው ሰራሽ ክፍሎች ይተካሉ። ይህም ዳሌው በበለጠ ምቾት እንዲንቀሳቀስ ሊረዳ ይችላል። የሕክምና ውሳኔዎች በምልክቶች ላይ ብቻ አይመሰረቱም። የምስል ምርመራ ውጤቶችና የጭን አጥንቱ ሁኔታ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሐኪሙ ተፈጥሯዊውን ዳሌ ማዳን እንደሚቻል ወይም መገጣጠሚያውን መተካት እንደሚሻል ለመወሰን ይረዳሉ።
በቬጅታኒ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል የሚሰጥ ልዩ የዳሌ ሕክምና
በታይላንድ የሚገኘው ቬጅታኒ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል የዳሌና ጉልበት ማዕከል (Hip and Knee Center) የዳሌ ችግሮችን ለማከም ልዩ አገልግሎት ይሰጣል። ማዕከሉ በመገጣጠሚያ መልሶ ግንባታና በዳሌ መገጣጠሚያ ምትክ ቀዶ ጥገና (Hip Arthroplasty) ልምድ ካላቸው የአጥንትና መገጣጠሚያ ሐኪሞች ጋር ይሰራል።
ኤ.ቪ.ኤን (AVN) የዳሌ መገጣጠሚያ ሲጎዳ የሕክምና ዕቅዱ በምልክቶች፣ በምስል ምርመራ ውጤቶችና በአጥንቱ ጉዳት ደረጃ ላይ ተመስርቶ ይዘጋጃል። የጭን አጥንቱን ክብ ክፍል መጠበቅ የሚቻል ከሆነ አጥንቱን ለማዳን የሚያግዙ ሕክምናዎች ሊታሰቡ ይችላሉ። በሽታው እየጨመረ ከባድ የመገጣጠሚያ ጉዳት ካስከተለ የዳሌ መገጣጠሚያ ምትክ ቀዶ ጥገና ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸውን የቀዶ ጥገና ዘዴዎች ጨምሮ አማራጭ ሊሆን ይችላል።
ሕክምናው በሚደረግበትና በማገገሚያ ወቅት ታካሚዎች ህመምን ለመቀነስ፣ የዳሌ እንቅስቃሴን ለማሻሻልና ወደ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ለመመለስ የሚረዳ ክትትል ያገኛሉ።
ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ወደ አጥንት መፍረስና የመገጣጠሚያ ጉዳት ሊያድግ ይችላል
ተገቢው ሕክምና ካልተደረገ የተጎዳው አጥንት እየደከመ ሊሄድ ይችላል። በጊዜ ሂደት የጭን አጥንቱ ክብ ቅርጽ ሊጠፋና በመጨረሻም ሊፈርስ ይችላል። ይህ ሲከሰት የዳሌ መገጣጠሚያው ወለል ያልተስተካከለ ይሆናል።
የመገጣጠሚያው ጉዳት እየባሰ ሲሄድ ህመምና መደንደን ሊጨምሩ ይችላሉ፤ መራመድና ዳሌን ማንቀሳቀስም ይበልጥ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። የመገጣጠሚያው ወለል መጎዳት ሁለተኛ ደረጃ አርትራይተስን (Secondary Osteoarthritis) ሊያስከትል ይችላል። የጭን አጥንቱ ክብ ክፍል ከፈረሰ በኋላ ተፈጥሯዊውን የዳሌ መገጣጠሚያ ለማዳን የሚደረጉ ሕክምናዎች ተስማሚ ላይሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ከባድ የመገጣጠሚያ ጉዳት ከመፈጠሩ በፊት ኤ.ቪ.ኤንን (AVN) ማወቅ የተለያዩ የሕክምና አማራጮችን ለመገምገም አስፈላጊ ነው።
በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች
የዳሌ አጥንት የደም አቅርቦት መቋረጥ/ ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ያለ ሕክምና በራሱ ሊድን ይችላል?
አጥንቱ ከተጎዳ በኋላ ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ብዙውን ጊዜ በራሱ አይድንም። በሽታው ከሰው ወደ ሰው በተለያየ ፍጥነት ሊብስ ይችላል። ስለዚህ ትክክለኛ ምርመራ በሽታው ያለበትን ደረጃና ተስማሚ የሕክምና አማራጮችን ለመወሰን አስፈላጊ ነው።
ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ያለበት ሰው ሁልጊዜ የዳሌ መገጣጠሚያ ምትክ ቀዶ ጥገና ማድረግ ያስፈልገዋል?
አይ። ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ያለባቸው ታካሚዎች ሁሉ የዳሌ መገጣጠሚያ ምትክ ቀዶ ጥገና አያስፈልጋቸውም። የጭን አጥንቱ ክብ ክፍል ከመፍረሱ በፊት በሽታው ከታወቀ ተፈጥሯዊውን መገጣጠሚያ ለማዳን የሚያግዙ ሕክምናዎች ሊታሰቡ ይችላሉ። የመገጣጠሚያው መፍረስ ወይም ጉዳት ከባድ ሲሆን ግን የመገጣጠሚያ ምትክ ቀዶ ጥገና በብዛት ይታሰባል።
ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ሁለቱንም ዳሌዎች ሊጎዳ ይችላል?
አዎ። ኤ.ቪ.ኤን (AVN) አንድን ዳሌ ወይም ሁለቱንም ዳሌዎች ሊጎዳ ይችላል። ምልክቶች በአንድ ወገን ብቻ ቢኖሩም የምስል ምርመራ በሌላኛው ዳሌ ላይም ለውጦች መኖራቸውን አንዳንድ ጊዜ ሊያሳይ ይችላል።
ኤ.ቪ.ኤን (AVN) ያለበት ሰው መራመድ ወይም የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላል?
ይህ በበሽታው ደረጃና በዳሌው ሁኔታ ላይ ይመሰረታል። እንደ መሮጥና መዝለል ያሉ በዳሌ ላይ ተደጋጋሚ ግጭትና ጫና የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን መቀነስ ሊያስፈልግ ይችላል። ሐኪም ወይም የአካል ሕክምና ባለሙያ የትኞቹ እንቅስቃሴዎች ተስማሚ እንደሆኑና በተጎዳው እግር ላይ ምን ያህል ክብደት ማሳረፍ ደህንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ ሊመክር ይችላል።
ኤ.ቪ.ኤን (AVN) በምን ያህል ፍጥነት ይባባሳል?
ለሁሉም ታካሚዎች የሚሰራ አንድ የተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ የለም። በሽታው የሚባባስበት ፍጥነት በተጎዳው አጥንት መጠንና ጉዳቱ በየትኛው አካባቢ ላይ እንደተፈጠረ ይወሰናል። መደበኛ የሐኪም ክትትልና የምስል ምርመራዎች በጊዜ ሂደት በአጥንቱ ላይ የሚከሰቱ ለውጦችን ለመከታተል ይረዳሉ።
ለበለጠ መረጃ ያግኙን
የዳሌና ጉልበት ማዕከል (Hip and Knee Center) ቬጅታኒ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል
ስልክ፦ (+66) 2-734-0000 Ext. 2222 የአማርኛ ስልክ መስመር: (+66) 90-907-2560
Medically Reviewed by
DR. WACHARA MANEERATROJ
Orthopedics
Total Joint Reconstruction (Arthroplasty)
Readers’ Rating
0.0 out of 5 stars (based on 0 reviews)