የጡት ካንሰር ግንዛቤ ወር፦ የራስዎን የአደጋ ተጋላጭነት በመረዳት ይጀምሩ

የጤና መረጃዎች

ጥቅምት የጡት ካንሰር ግንዛቤ ወር (Breast Cancer Awareness Month) ሲሆን ምንም የሚታዩ ምልክቶች ወይም የቤተሰብ የጡት ካንሰር ታሪክ ባይኖርዎትም ለጡትዎ ጤና ትኩረት መስጠት እንዳለብዎ የሚያስታውስ አስፈላጊ ጊዜ ነው። ዕድሜዎ፣ የጤና ታሪክዎ እና ከዚህ በፊት የተደረጉልዎት የጡት ምርመራዎች ውጤት ሐኪሞች የጡት ካንሰር ምርመራን (Breast Cancer Screening) መቼ መጀመር እንዳለብዎ እንዲወስኑ ይረዳሉ።

ጥቅምት፦ ለጡት ካንሰር ግንዛቤ ትኩረት የሚሰጥበት ወር

ብዙ ጊዜ ሰዎች የጡት ጤናን በተመለከተ ያላቸው ጥያቄዎች አንድ ነገር እስኪሰማቸው ወይም እስኪያስጨንቃቸው ድረስ ሳይመለሱ ይቆያሉ። በጥቅምት ወር የሚካሄዱ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ዘመቻዎች ሰዎች ቀድመው የሕክምና ምክር እንዲያገኙ፣ ምርመራ እንዲያደርጉ እና አስፈላጊ ሲሆን በጊዜው ሕክምና እንዲያገኙ ያበረታታሉ።

የግል የጡት ካንሰር ተጋላጭነትዎ ከቤተሰብ ታሪክ በላይ የሚመረኮዝ ነው

በቤተሰብዎ ውስጥ የጡት ካንሰር ታሪክ አለመኖሩ ለዚህ በሽታ ተጋላጭ አይደሉም ማለት አይደለም። ዕድሜዎ፣ የጡት ሕብረ ሕዋስ/ ቲሹ ጥግግት (Breast Density) እና ከዚህ በፊት ያጋጠሙዎት የጡት ችግሮች ሐኪምዎ ምን ዓይነት የምርመራ ዘዴ እንደሚያስፈልግዎ እንዲወስን ይረዳሉ።

ዕድሜ እና የጤና ታሪክ

የጡት ካንሰር የመከሰት ዕድል ከዕድሜ ጋር ይጨምራል። ቀደም ሲል የጡት በሽታ መኖሩ ወይም በጡት ባዮፕሲ (Breast Biopsy) ምርመራ ውስጥ ያልተለመዱ ሴሎች መገኘታቸውም ትኩረት ይፈልጋል። ከዚህ በፊት የተደረጉ የባዮፕሲ ውጤቶች ሐኪሞች እነዚህን ለውጦች በትክክል እንዲገመግሙ ይረዳሉ።

በልጅነት ወይም በወጣትነት ዕድሜ በደረት አካባቢ ለጨረር ሕክምና (Radiation Therapy) መጋለጥ ቀደም ብሎ የጡት ካንሰር ምርመራ ማድረግን ሊያስፈልግ ይችላል።

የቤተሰብ ታሪክ እና በዘር የሚተላለፉ የዘረመል/ ጂን (Gene) ለውጦች

በእናትም ሆነ በአባት በኩል ባለው ቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር፣ የኦቫሪ ካንሰር (Ovarian Cancer) ወይም ሌሎች የካንሰር ዓይነቶች ታሪክ መኖሩ የግል ተጋላጭነትን ለመገምገም አስፈላጊ ነው። ሐኪሞች የትኞቹ ዘመዶች በካንሰር እንደተያዙ እና በምን ዕድሜ እንደታወቀባቸው ይመለከታሉ።

በተለይም ብዙ ዘመዶች በወጣትነት ዕድሜያቸው በጡት ወይም በኦቫሪ ካንሰር ከተያዙ በዘር የሚተላለፍ የዘረመል/ ጂን (Gene) ለውጥ ሊኖር ይችላል። የዘረመል/ ጄኔቲክ አማካሪ (Genetic Counselor) የቤተሰብ ታሪክዎን ይገመግማል፤ እንዲሁም ቢ.አር.ሲ.ኤ 1 (BRCA1) እና ቢ.አር.ሲ.ኤ 2 (BRCA2) በሚባሉ ጂኖች ላይ ያሉ ለውጦችን ለመፈተሽ የዘረመል/ ጄኔቲክ ምርመራ (Genetic Testing) ማድረግ ለምርመራ ወይም ለሕክምና ውሳኔዎች ይጠቅም እንደሆነ ያብራራል።

የሆርሞን እና የመውለድ ታሪክ

የወር አበባ ከ12 ዓመት በፊት መጀመር ወይም ከ55 ዓመት በኋላ ማረጥ (Menopause) መድረስ ሰውነት ለኤስትሮጅን (Estrogen) ሆርሞን ለረዥም ጊዜ እንዲጋለጥ ያደርጋል። ይህ ረዥም ጊዜ የሚቆይ የሆርሞን ተጋላጭነት የጡት ካንሰር አደጋን ይጨምራል።

የመጀመሪያ ልጅን ከ30 ዓመት በኋላ መውለድም ከፍ ያለ ተጋላጭነት ጋር ሊያያዝ ይችላል። ከማረጥ በኋላ ኤስትሮጅንን ከፕሮጀስትሮን (Progesterone) ጋር የሚያካትት የሆርሞን ሕክምናም ሐኪሞች ሲገመግሙ ከሚያስቡባቸው ምክንያቶች አንዱ ነው።

የአኗኗር ዘይቤ እና የሰውነት ክብደት

አልኮል መጠጣት የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ይጨምራል፤ የሚጠጣው አልኮል መጠን በጨመረ ቁጥር አደጋውም ይጨምራል። በተጨማሪም በመደበኛነት አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ከማረጥ በኋላ ከመጠን በላይ ክብደት መኖር ተጋላጭነትን ይጨምራሉ።

የሐኪም ምርመራ የሚያስፈልጋቸው የጡት ለውጦች

አዲስ የጡት እብጠት፣ ከጡት ጫፍ ፈሳሽ መውጣት፣ በጡት ጫፍ ላይ ቁስል መፈጠር ወይም የጡት ቅርጽ መለወጥ የሕክምና ግምገማ ይፈልጋል።

ትኩረት መስጠት ያለባቸው ምልክቶች፦

  • በጡት ወይም በብብት ሥር አዲስ እብጠት መታየት
  • በጡት ማንኛውም ክፍል ውፍረት ወይም እብጠት መፈጠር
  • የጡት መጠን ወይም ቅርጽ መለወጥ
  • የቆዳ መጠርጠር ወይም ወደ ውስጥ መጎተት
  • ቀድሞ ወደ ውጭ የነበረ የጡት ጫፍ በቅርቡ ወደ ውስጥ መግባት
  • ከጡት ማጥባት ጋር የማይያያዝ ፈሳሽ ከጡት ጫፍ መውጣት፤ በተለይም ደም የተቀላቀለበት ፈሳሽ
  • በጡት ጫፍ ዙሪያ የማይጠፋ መቅላት፣ ቆዳ መላጥ፣ ቁስል ወይም ሽፍታ
  • በአንድ ቦታ የሚቆይ ወይም የማይጠፋ አዲስ ሕመም

እነዚህ ለውጦች ሁሉ የጡት ካንሰር አለ ማለት አይደሉም። ካንሰር ያልሆኑ ሌሎች ችግሮችም ተመሳሳይ ምልክቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። የሐኪም ምርመራ ምክንያቱን ለመለየት ይረዳል።

አዲስ የጡት ለውጥ ከተመለከቱ ቀጣዩን መደበኛ ምርመራ እስኪደርስ መጠበቅ የለብዎትም። በቅርቡ ያደረጉት ምርመራ መደበኛ ውጤት ቢኖረውም አዲሱን ለውጥ በሐኪም መገምገም አለበት።

ምልክቶች ከመታየታቸው በፊት የጡት ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው

ዓመታዊ የጡት ማሞግራፊ (Mammography) ምርመራ ምልክቶች በሌላቸው ሴቶች ውስጥ የጡት ካንሰርን ቀድሞ ለመለየት ይረዳል። አማካይ የአደጋ ተጋላጭነት ላላቸው ሴቶች ምርመራውን ከ40 ዓመት ጀምሮ ማድረግ ይመከራል፤ ሆኖም በምርመራዎች መካከል የሚኖረው ጊዜ እንደ ግለሰቡ ሁኔታ ይለያያል።

ጠንካራ የቤተሰብ የካንሰር ታሪክ፣ ጉዳት የሚያስከትል የቢ.አር.ሲ.ኤ 1 (BRCA1) ወይም ቢ.አር.ሲ.ኤ 2 (BRCA2) ጂን ለውጥ፣ ወይም በወጣትነት ዕድሜ ለደረት ጨረር መጋለጥ ምርመራን ከ40 ዓመት በፊት መጀመር እንዲያስፈልግ ሊያደርግ ይችላል።

ከ40 ዓመት ጀምሮ ላሉ ሴቶች ማሞግራፊ ዋናው የማጣሪያ ምርመራ ነው። የጡት አልትራሳውንድ (Breast Ultrasound) የተወሰነ አካባቢን በበለጠ ዝርዝር ለመመርመር ይረዳል፤ የጡት ኤም.አር.አይ (Breast MRI) ደግሞ በወጣት ዕድሜ ላይ ያሉና ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ሴቶች ምርመራን ለማሟላት ሊጠቅም ይችላል።

የጡት ማሞግራፊ (Mammography)

ማሞግራፊ የጡት ቲሹን ለመመርመር ዝቅተኛ መጠን ያለውን የኤክስ-ሬ ጨረር (X-ray) ይጠቀማል። እብጠት በእጅ ከመዳሰሱ በፊት ትናንሽ ዕጢዎችን እና ቀደምት የጡት ካንሰር ምልክት ሊሆኑ የሚችሉ ጥቃቅን የካልሲየም ክምችቶችን (Calcium Deposits) ለመለየት ይረዳል።

ሐኪሞች በጊዜ ሂደት የተከሰቱ ለውጦችን ለመመልከት አዲሱን ምስል ከቀደሙት የማሞግራፊ ምስሎች ጋር ያነጻጽራሉ። የቀድሞ ምስሎችንና የምርመራ ሪፖርቶችን ይዞ መሄድ ለምስል ትንተና ባለሙያው ጠቃሚ መረጃ ይሰጣል።

የጡት አልትራሳውንድ (Breast Ultrasound)

የጡት አልትራሳውንድ የጡት ሕብረ ሕዋሳትን/ቲሹን (Tissue) ምስል ለማዘጋጀት የድምፅ ሞገዶችን ይጠቀማል። እንደ እብጠት ወይም በማሞግራፊ ምርመራ የታየ ልዩ አካባቢ ያለ ክፍልን በቅርበት ለመመርመር እና ፈሳሽ የያዘ ሲስት (Cyst) ከጠንካራ እጢ (Solid Mass) ለመለየት ይረዳል።

እንደ የጡት ሕብረ ሕዋስ/ ቲሹ ጥግግትና (Breast Density) ሌሎች የምርመራ ግኝቶች ሁኔታ ሐኪሞች አልትራሳውንድን ከማሞግራፊ ጋር አብሮ እንዲደረግ ሊመክሩ ይችላሉ።

የጡት ኤም.አር.አይ (Breast MRI)

የጡት ኤም.አር.አይ (Breast MRI) የጡት ሕብረ ሕዋስ/ ቲሹን ዝርዝር ምስል ለማግኘት መግነጢሳዊ መስክንና የሬዲዮ ሞገዶችን ይጠቀማል። ከፍተኛ ተጋላጭነት ላላቸው ሰዎች ሐኪሞች ኤም.አር.አይን/ MRI ከማሞግራፊ ጋር በአንድ የምርመራ ዕቅድ ውስጥ ሊያካትቱ ይችላሉ።

ኤም.አር.አይ/ MRI ተጨማሪ ግምገማ የሚፈልጉ ግኝቶችንም ለመመርመር ይረዳል። ይህ ምርመራ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም የሚለው በግለሰቡ ተጋላጭነት፣ ዕድሜ፣ የጡት ማሳደጊያ ቀዶ ጥገና ታሪክ፣ የቀድሞ የምርመራ ውጤቶች እና የምርመራው ዓላማ ላይ ይመረኮዛል።

ለጡት ጤና ምርመራ ቀጠሮ መዘጋጀት

ወደ ሐኪም ቀጠሮ ሲሄዱ የቀድሞ የምስል ምርመራዎችንና የሕክምና ውጤቶችን ይዘው ይሂዱ። ከቤተሰብ ታሪክ ጋር በተያያዘ የትኛው ዘመድ በምን ዓይነት ካንሰር እንደተያዘና በምን ዕድሜ እንደታወቀበት መመዝገብ ጠቃሚ ነው።

  • የቀድሞ ምርመራዎች፦ የማሞግራፊ፣ የአልትራሳውንድ ወይም ኤም.አር.አይ ሪፖርቶችን እንዲሁም የባዮፕሲ ውጤቶችን ይዘው ይሂዱ።
  • በቤተሰብ ውስጥ ያለ የካንሰር ታሪክ፦ ዘመዱ ምን ዓይነት ዝምድና እንዳለው፣ የካንሰሩ ዓይነት እና ካንሰሩ የታወቀበት ዕድሜ
  • መድኃኒቶችና የሆርሞን ሕክምናዎች፦ አሁን የሚወስዷቸውን መድኃኒቶች ስም፣ ከማረጥ ጋር የተያያዘ የሆርሞን ሕክምናን ጨምሮ
  • አዲስ የጡት ለውጦች፦ ምን እንደተለወጠ፣ መቼ እንደጀመረ እና ለውጡ እየቀጠለ ወይም እየባሰ እንደሆነ ያስታውሱ።

የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ በየቀኑ ማድረግ የሚቻሉ ነገሮች

  • በመደበኛነት አካላዊ እንቅስቃሴ ያድርጉ፦ ፈጣን የእግር ጉዞ፣ ብስክሌት መንዳት እና ዋና መዋኘት የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሊረዱ ይችላሉ።
  • ጤናማ ክብደት ይጠብቁ፦ ከማረጥ በኋላ ከመጠን በላይ ክብደት መኖር የጡት ካንሰር አደጋን ይጨምራል። መደበኛ እንቅስቃሴና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ጤናማ ክብደትን ለመጠበቅ ይረዳሉ።
  • የአልኮል መጠጥን ይቀንሱ፦ የሚጠጡት መጠን በጨመረ ቁጥር የጡት ካንሰር አደጋ ይጨምራል። አልኮልን መቀነስ ወይም ሙሉ በሙሉ መተው ይህን አደጋ ለመቀነስ ይረዳል።
  • የማረጥ ዘመን የሆርሞን ሕክምናን ይገምግሙ፦ በሕክምናው ጥቅም፣ አደጋ እና የሚቆይበት ጊዜ ላይ ሐኪምዎን ያማክሩ። ሕክምናውን ከመቀየርዎ በፊት የሕክምና ምክር ያግኙ።

እነዚህ እርምጃዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስ ይረዳሉ፤ ሆኖም የጡት ምርመራን አይተኩም፤ እንዲሁም ካንሰር ፈጽሞ እንደማይከሰት ዋስትና አይሰጡም።

ከጥቅምት ወር በኋላም የጡት ጤናን መንከባከብ ይቀጥሉ

የጡት ካንሰር ግንዛቤ ወር ለጡት ጤና ትኩረት እንዲሰጥ ያበረታታል፤ ነገር ግን ምርመራና ተከታታይ ክትትል ዓመቱን ሙሉ መቀጠል አለባቸው። ግልጽ የምርመራ ዕቅድ መኖሩ ዓመታዊ ምርመራዎችን በጊዜው ለማድረግና አዲስ ምልክቶች ሲከሰቱ በቶሎ ምርመራ እንዲደረግ ይረዳል።

በቬጅታኒ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል የጡት ማዕከል (Breast Center) ምክክር ማድረግ የግል ተጋላጭነትዎን እና የሚያስፈልግዎትን ምርመራ በግልጽ ለመረዳት ይረዳል። የጡት ሕክምና ስፔሻሊስት የጤና ታሪክዎንና የቀድሞ የምርመራ ውጤቶችዎን በመገምገም ቀጣይ እርምጃዎችን ይመክራል።

በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች (FAQ)

የጡት ካንሰር ግንዛቤ ወር ምንድን ነው?

የጡት ካንሰር ግንዛቤ ወር በጥቅምት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር የጤና ግንዛቤ ዘመቻ ነው። ዓላማው ስለ ጡት ካንሰር ግንዛቤን ማሳደግ፣ ቅድመ-ምርመራን ማበረታታት፣ በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን መደገፍ እና የጡት ካንሰር ምርምርን ማበረታታት ነው።

ለምንድን ነው ጥቅምት የጡት ካንሰር ግንዛቤ ወር የሆነው?

የጥቅምት ወር ከጡት ካንሰር ግንዛቤ ጋር መያያዙ እ.እ.አ በ1985 በአሜሪካ የተጀመረ ዘመቻ ይጀምራል። ዘመቻው ማሞግራፊንና ቅድመ-ምርመራን ለማበረታታት የተካሄደ ሲሆን በኋላ ወደ ወር ሙሉ የሚቆይ ዘመቻ አደገ። ዛሬ በዓለም ዙሪያ ያሉ ድርጅቶች በየጥቅምቱ በዚህ ዘመቻ ይሳተፋሉ።

በጡት ካንሰር ግንዛቤ ወር እንዴት መሳተፍ እችላለሁ?

ስለ ጡት ካንሰር የአደጋ ምክንያቶችና የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ይማሩ። ስለሚመከሩ የምርመራ ዘዴዎች መረጃ ያግኙ፣ የሚወዷቸውን ሰዎችም ለጡት ጤናቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ ያበረታቱ። እንዲሁም ታማኝ የጤና መረጃን ማጋራት፣ የግንዛቤ ዘመቻዎችን መደገፍ እና እንደ የግል ተጋላጭነትዎ መሠረት የጡት ምርመራን መቼ መጀመር እንዳለብዎ ሐኪምዎን ማማከር ይችላሉ።

በቤተሰቤ ውስጥ ማንም የጡት ካንሰር ካልያዘው ምርመራ ማድረግ ያስፈልገኛል?

አዎ። የቤተሰብ የጡት ካንሰር ታሪክ አለመኖሩ ምርመራ እንዳያስፈልግዎ አያደርግም። ዕድሜ፣ የጡት ሕብረ ሕዋስ/ ቲሹ ጥግግትና (Breast Density) እና የጤና ታሪክም ተጋላጭነትን ይወስናሉ። ሐኪሞች ምርመራው መቼ መጀመር እንዳለበትና በምን ያህል ጊዜ መደገም እንዳለበት ለመወሰን እነዚህን ሁኔታዎች ይመለከታሉ።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያግኙን

የጡት ማዕከል (Breast Center)
ቬጅታኒ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል

ስልክ፦ (+66) 2-734-0000 Ext. 2715፣ 2716

የአማርኛ ስልክ መስመር: (+66) 90-907-2560

Medically Reviewed by

DR. ALISARA CHAT-ISSARAWACH
DR. ALISARA CHAT-ISSARAWACH

Surgery

Surgical Oncology and Breast Surgery

Readers’ Rating

0.0 out of 5 stars (based on 0 reviews)