ከአደጋ፣ ከመውደቅ ወይም ከአንገትና ትከሻ ጉዳት በኋላ የሚቀጥል የክንድ ድካም ሁልጊዜ በጡንቻ ወይም በመገጣጠሚያ ችግር ብቻ የሚከሰት አይደለም። የነርቭ ጉዳትም ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የብራኪያል ፕሌክሰስ ጉዳት (Brachial Plexus Injury) የመደንዘዝ፣ የህመም እና ክንድን ለማንቀሳቀስ የመቸገር ምልክቶችን ሊያስከትል ይችላል። ይህ የነርቭ መረብ ከአከርካሪ አጥንት የሚመጡ መልዕክቶችን ወደ ትከሻ፣ ክንድ እና እጅ ያስተላልፋል።
የክንዱ ማገገም ምን ያህል እንደሚሆን በአብዛኛው ጉዳቱ በየትኛው የነርቭ ክፍል ላይ እንደተፈጠረ እና ጉዳቱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይወሰናል።
የብራኪያል ፕሌክሰስ ጉዳት (Brachial Plexus Injury) የክንድን ተግባር እንዴት ይጎዳል?
ብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) የአከርካሪ ነርቭ ስርዓትን ከትከሻ፣ ከክንድ እና ከእጅ እንቅስቃሴና ስሜት ጋር የሚያገናኝ የነርቮች መረብ ነው።
ይህ የነርቭ መረብ ሲጎዳ የሚከተሉት ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፦
ክንድን ወደ ላይ ለማንሳት መቸገር
ክርንን ለማጠፍ መቸገር
አንጓን ለማንቀሳቀስ መቸገር
እቃዎችን በእጅ ለመያዝ መቸገር
ህመም ወይም መደንዘዝ
የስሜት ለውጥ
የጉዳቱ ተፅዕኖ በነርቩ ላይ በደረሰው ጉዳት መጠን ላይ ይመሰረታል። የተዘረጋ ወይም የተጫነ ነርቭ ሊያገግም ይችላል፤ ነገር ግን የተቀደደ ነርቭ ወይም ከአከርካሪ አጥንት የተነጠለ የነርቭ ስር የበለጠ ከባድና ዘላቂ የእንቅስቃሴና የስሜት ችግር ሊያስከትል ይችላል።
የነርቭ ጉዳቱ የተፈጠረበት ቦታ ምልክቶቹን እንዴት ይወስናል?
የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት ምልክቶች ከቀላል የስሜት ለውጥ እስከ ከፍተኛ የክንድ ተግባር ማጣት ድረስ ሊለያዩ ይችላሉ።
የተለመዱ ምልክቶች፦
የክንድ ድካም: ክንድን ወደ ላይ ለማንሳት፣ ክርንን ለማጠፍ፣ አንጓን ለማንቀሳቀስ ወይም እቃዎችን ለመያዝ መቸገር።
መደንዘዝ ወይም መወጋገር: በትከሻ፣ በክንድ፣ በክንድ የታችኛው ክፍል፣ በእጅ ወይም በጣቶች ላይ የስሜት መቀነስ ወይም ለውጥ።
የነርቭ ህመም: የሚያቃጥል፣ የሚወጋ ወይም እንደ ኤሌክትሪክ የሚሰማ ህመም፣ ከትከሻ ወደ ክንድ ወይም ወደ እጅ ሊሰራጭ ይችላል።
የቅንጅት ችግር: በተለይ የእጅና የጣቶች ትክክለኛ ቁጥጥር በሚያስፈልጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ መቸገር።
የእንቅስቃሴ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ማጣት: ከባድ የነርቭ ጉዳት በክንዱ አንድ ክፍል ላይ ከፍተኛ ድካም ወይም ሽባነት ሊያስከትል ይችላል።
የላይኛው ብራኪያል ፕሌክሰስ (Upper Brachial Plexus) ጉዳት
በላይኛው የብራኪያል ፕሌክሰስ (Upper Brachial Plexus) ክፍል ላይ የሚደርስ ጉዳት በተለምዶ ትከሻና የላይኛውን ክንድ የሚቆጣጠሩ ነርቮችን ይጎዳል።
በተለይ በC5–C6 የነርቭ ስሮች ላይ ጉዳት ከደረሰ ታካሚው፦
ክንዱን ወደ ላይ ለማንሳት
ክንዱን ለማዞር
ክርኑን ለማጠፍ ሊቸገር ይችላል። የእጅ ተግባር ግን በአንፃራዊነት ሊጠበቅ ይችላል።
የታችኛው ብራኪያል ፕሌክሰስ (Lower Brachial Plexus) ጉዳት
የታችኛው ፕሌክሰስ (Lower Brachial Plexus) ጉዳት በተለምዶ የክንድ የታችኛውን ክፍል፣ አንጓንና እጅን ይጎዳል።
በC8–T1 የነርቭ ስሮች ላይ ጉዳት ሲደርስ፦
የእጅ መያዣ ኃይል ሊቀንስ
የጣቶች እንቅስቃሴ ትክክለኛነት ሊቀንስ
በክንድ ወይም በእጅ ላይ የስሜት ለውጥ ሊፈጠር ይችላል።
የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳቶች ዓይነቶች
የጉዳቱ ዓይነት በነርቩ ላይ ምን እንደደረሰ ያሳያል።
የነርቭ መዘርጋት (Stretch Injury): ነርቩ ሳይቀደድ ይዘረጋል።
የነርቭ መቀደድ (Nerve Rupture): ነርቩ ይቀደዳል።
ከአከርካሪ ነርቭ ስር መነጠል (Avulsion): የነርቭ ስሩ ከአከርካሪ አጥንት ይነጠላል።
እነዚህ ልዩነቶች የነርቩን የማገገም እድል እና የሚያስፈልገውን ሕክምና ይወስናሉ።
የብራኪያል ፕሌክሰስ የመዘርጋት ጉዳት (Brachial Plexus Stretch Injury)
ነርቭ ከመደበኛ የመዘርጋት መጠኑ በላይ ሲዘረጋ ወደ ክንድ የሚሄዱ የነርቭ ምልክቶችን ሊያስተጓጉል ይችላል፤ ነገር ግን ነርቩ ሙሉ በሙሉ ሳይቀደድ ይቀራል።
ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶች፦
ድካም
መደንዘዝ
መወጋገር
የእንቅስቃሴ መቀነስ
አንዳንድ የመዘርጋት ጉዳቶች ቀስ በቀስ ሊያገግሙ ይችላሉ። ሆኖም የማገገሚያው ጊዜ በጉዳቱ ክብደት ላይ ይመሰረታል።
የብራኪያል ፕሌክሰስ ነርቭ መቀደድ (Brachial Plexus Nerve Rupture)
የነርቩ አንድ ክፍል ሲቀደድ ወደ ክንድ የሚሄዱ የነርቭ መልዕክቶች በመደበኛው ሁኔታ ላይተላለፉ ይችላሉ።
እንደ ጉዳቱ ቦታና ክብደት ታካሚው፦
ድካም
መደንዘዝ
የክንድ አንድ ክፍልን ለማንቀሳቀስ መቸገር ሊያጋጥመው ይችላል።
ከባድ የነርቭ መቀደድ ነርቩ በራሱ ማገገም የማይችል ከሆነ የነርቭ ጥገና ወይም የመልሶ ግንባታ ቀዶ ጥገና ሊያስፈልግ ይችላል።
የብራኪያል ፕሌክሰስ አቫልሽን ጉዳት (Brachial Plexus Avulsion)
አቫልሽን/ Avulsion ማለት የነርቭ ስሩ ከአከርካሪ አጥንት ተነጥሎ መውጣት ነው። ይህ ከሁሉም የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳቶች በጣም ከባድ ዓይነት ነው።
የነርቭ ስሩ ከአከርካሪ አጥንት ከተነጠለ እንደተዘረጋ ወይም እንደተቀደደ ነርቭ በተመሳሳይ መንገድ ማገገም አይችልም።
በእንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች የነርቭ ባለሙያ ሐኪሞች እንደ የነርቭ ማስተላለፍ (Nerve Transfer) ያሉ ቴክኒኮችን በመጠቀም የተወሰኑ የክንድ እንቅስቃሴዎችን ለመመለስ ሊሞክሩ ይችላሉ።
የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት የተለመዱ መንስኤዎች
አብዛኛዎቹ በአደጋ የሚፈጠሩ ጉዳቶች አንገትና ትከሻ በተቃራኒ አቅጣጫ በኃይል ሲጎተቱ ወይም በነርቮች ላይ ድንገተኛ ጫና ሲደረግ ይፈጠራሉ።
የተለመዱ መንስኤዎች፦
የሞተርሳይክል እና የተሽከርካሪ አደጋዎች: ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ግጭቶች በአንገትና በትከሻ አካባቢ ያሉ ነርቮችን ሊዘረጉ ወይም ሊቀድዱ ይችላሉ።
የስፖርት ጉዳቶች: የግጭት ስፖርቶችና ከፍተኛ ተፅእኖ ያላቸው እንቅስቃሴዎች በአንገትና በትከሻ አካባቢ ያሉ ነርቮችን በድንገት ሊዘረጉ ወይም ሊጫኑ ይችላሉ።
መውደቅ: በትከሻ ወይም በአንገት ላይ በኃይል መውደቅ ነርቮቹን ሊዘረጋ ወይም ሊጫን ይችላል።
ጥልቅ ቁስሎች: በአንገት ወይም በትከሻ አካባቢ የሚደርሱ ከባድ መቁሰሎች በቀጥታ የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ነርቮችን ሊጎዱ ይችላሉ።
በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ጉዳት: ከባድ ወሊድ በተለይም የሕፃኑ ትከሻ በወሊድ ወቅት ሲጣበቅ የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ነርቮች ሊዘረጉ እና የብራኪያል ፕሌክሰስ ሽባነት (Brachial Plexus Palsy) ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ተመሳሳይ ዓይነት አደጋ ቢደርስም የነርቭ ጉዳቱ አይነትና ክብደት ከሰው ወደ ሰው ሊለያይ ይችላል። ከጉዳት በኋላ የሚቀጥል ድካም ወይም የስሜት ማጣት ስለዚህ የተጎዱትን ነርቮች ለመለየት ተጨማሪ ምርመራ ሊያስፈልገው ይችላል።
ሐኪሞች የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳትን እንዴት ይመረምራሉ?
የክንድ ድካም ብቻ የጉዳቱን ሙሉ መጠን ለማሳየት በቂ አይደለም። የድካሙ አካባቢ፣ የመደንዘዙ ሁኔታ እና በሪፍሌክስ ላይ የሚታዩ ለውጦች የትኛው የነርቭ ክፍል እንደተጎዳ ሊጠቁሙ ይችላሉ።
ሐኪሞች የምርመራ ውጤቶችን ከሚከተሉት ምርመራዎች ጋር ያጣምራሉ፦
አካላዊ ምርመራ
በአንዳንድ ሁኔታዎች ትከሻና ክርን ደካማ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን የአንጓና የእጅ ተግባር መደበኛ ሆኖ ሊቆይ ይችላል። በሌሎች ሁኔታዎች ድካሙ ወደ ታችኛው የክንድ ክፍል ሊሰራጭ ይችላል።
ሐኪሞች የጉዳቱን ቦታ ለማወቅ የጡንቻ ኃይልን፣ ሪፍሌክስን እና ስሜትን ይመረምራሉ።
ማግኔቲክ ሬዞናንስ ኢሜጂንግ/ ኤም.አር.አይ (MRI)
ኤም. አር. አይ (MRI) የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ነርቮችንና በዙሪያቸው ያሉ ሕብረ ሕዋሳትን በዝርዝር ለማየት ይረዳል።
ሐኪሞች ኤም.አር.አይ (MRI) ለሚከተሉት ሊጠቀሙ ይችላሉ፦
የነርቭ ጉዳትን ለመለየት
እብጠትን ለማየት
የጠባሳ ሕብረ ሕዋስን ለማየት
ምልክቶቹን የሚያስከትሉ ሌሎች ለውጦችን ለመለየት
የሕክምና ዕቅድን ለማዘጋጀት
ኤሌክትሮማዮግራፊ (ኢ.ኤም.ጂ /EMG) እና የነርቭ ምልክት ፍጥነት ምርመራ
ኤሌክትሮማዮግራፊ ( ኢ. ኤም. ጂ /EMG) እና የነርቭ ማስተላለፊያ ጥናቶች (Nerve Conduction Studies) ነርቮችና ጡንቻዎች ከጉዳት በኋላ ምን ያህል በትክክል እየሰሩ እንደሆነ ይገመግማሉ።
እነዚህ ምርመራዎች፦
የተጎዱ ነርቮችን ለመለየት
የነርቭ ጉዳቱን መጠን ለመገምገም
ከጊዜ በኋላ የነርቭ ተግባር እየተመለሰ መሆኑን ለመከታተል ይረዳሉ።
ኤክስ-ሬ (X-ray) ወይም ሲ.ቲ ማይሎግራፊ (CT Myelography)
ኤክስ- ሬ (X-ray) በአንገትና በትከሻ አካባቢ ያሉ ስብራቶችን ወይም ሌሎች የአጥንት ጉዳቶችን ለመለየት ይረዳል። በበለጠ ከባድ ሁኔታዎች ሲ.ቲ ማይሎግራፊ (CT Myelography) በአከርካሪ አጥንት አቅራቢያ ያለውን የነርቭ ስር ጉዳት፤ በተለይም አቫልሽን/ Avulsion ጉዳትን በበለጠ ዝርዝር ለማየት ሊረዳ ይችላል።
የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት የሕክምና አማራጮች
የሕክምና ዕቅዱ በነርቭ ጉዳቱ መጠን እና በተጎዳው ክንድ ውስጥ ቀሪ ተግባር ላይ ይመሰረታል።
የነርቭ ማገገም ምልክቶች፣ የጉዳቱ ቦታ እና ጉዳቱ ከደረሰ ጀምሮ ያለፈው ጊዜ ተሀድሶ ብቻ በቂ መሆኑን ወይም የነርቭ ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልግ ለመወሰን ይረዳሉ።
ተሀድሶ/ ማገገሚያ (Rehabilitation) እና ያለ ቀዶ ጥገና የሚደረግ ሕክምና
የተዘረጋ ወይም የተጫነ ነርቭ አንዳንድ ጊዜ ያለ ቀዶ ጥገና ማገገም ይችላል።
በዚህ ወቅት የአካል ተሀድሶ/ ማገገሚያ (Rehabilitation) የሚከተሉትን ይረዳል፦
ትከሻ፣ ክርን፣ አንጓና እጅ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ
የመገጣጠሚያ መደንዘዝን እና የጡንቻ መጠርዘርን መከላከል
አሁንም እየሰሩ ያሉ ጡንቻዎችን ማጠናከር
የእጅ ቅንጅትንና የዕለት ተዕለት ተግባራትን መደገፍ
ህመምንና የስሜት ለውጦችን መቆጣጠር
የነርቭና የጡንቻ ተግባር መመለስን መከታተል
ነርቮች በዝግታ ስለሚያገግሙ ሐኪሞች ለብዙ ወራት የጡንቻ ኃይልን፣ ስሜትን፣ እንቅስቃሴን እና የኢ.ኤም.ጂ /EMG ውጤቶችን ሊከታተሉ ይችላሉ።
የብራኪያል ፕሌክሰስ ቀዶ ጥገና (Brachial Plexus Surgery)
ከባድ የነርቭ ጉዳት ከተሀድሶ/ ማገገሚያ (Rehabilitation) እና ከጊዜ በኋላም የክንድ እንቅስቃሴ እንዲገደብ ሊያደርግ ይችላል።
በእነዚህ ሁኔታዎች ቀዶ ጥገና መደበኛ የነርቭ ምልክት እየደረሰባቸው ያልሆኑ ጡንቻዎች እንደገና የነርቭ ምልክት እንዲያገኙ ሊረዳ ይችላል።
ሐኪሞች የሚከተሉትን ይገመግማሉ፦
የተጎዱት ነርቮች
የቀረው የክንድ ተግባር
ከጉዳቱ ጀምሮ ያለፈው ጊዜ
የነርቭ ጥገና (Nerve Repair)
ነርቩ በንጹህ ሁኔታ ከተቀደደ እና የነርቭ ሕብረ ሕዋስ መጥፋት ትንሽ ከሆነ ሐኪሞች ሁለቱን የነርቭ ጫፎች በቀጥታ እንደገና ሊያገናኙ ይችላሉ።
በዚህ ሁኔታ የነርቭ ግራፍት (graft) አያስፈልግም። አዲስ የነርቭ ፋይበሮች በተጠገነው ክፍል በኩል እያደጉ ወደ ጡንቻዎች ሊደርሱ ይችላሉ።
የነርቭ ግራፍቲንግ (Nerve Grafting)
የጉዳቱ ምክንያት የነርቩን አንድ ክፍል ከጎዳ፣ ሁለቱ ጤናማ የነርቭ ጫፎች በቀጥታ እንዲገናኙ በጣም ርቀት ሊኖራቸው ይችላል።
በዚህ ሁኔታ ሐኪሞች ከሌላ የሰውነት ክፍል የተወሰደ ጤናማ የነርቭ ክፍል በመጠቀም በሁለቱ ጫፎች መካከል ያለውን ክፍተት ሊያገናኙ ይችላሉ።
ከዚያ አዲስ የነርቭ ፋይበሮች በግራፍቱ ውስጥ እያደጉ ወደ ተፈለጉት ጡንቻዎች ይሄዳሉ።
የነርቭ ማስተላለፍ (Nerve Transfer)
ከባድ ጉዳት ዋናውን የነርቭ መንገድ መጠቀም የማይቻል ሊያደርገው ይችላል።
በዚህ ሁኔታ ሐኪሞች በአቅራቢያው ያለ ጤናማና እየሰራ ያለ የነርቭ ቅርንጫፍ ወስደው የደከመውን ጡንቻ ከሚቆጣጠረው ነርቭ ጋር ሊያገናኙት ይችላሉ።
ይህ የነርቭ ምልክቶች ወደ ጡንቻው የሚደርሱበትን መንገድ ያሳጥራል፤ እንደ፦
ትከሻን ወደ ላይ ማንሳት
ክርንን ማጠፍ ያሉ እንቅስቃሴዎች እንዲመለሱ ሊረዳ ይችላል።
ከብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት በኋላ ጊዜ ለምን አስፈላጊ ነው?
ጊዜ የተጎዱ ነርቮችና እነሱ የሚቆጣጠሯቸው ጡንቻዎች የማገገም እድል ላይ ትልቅ ተፅእኖ አለው።
ጡንቻዎች ለረጅም ጊዜ መደበኛ የነርቭ ምልክት ካላገኙ ተግባራቸውን የመመለስ ችሎታቸው ቀስ በቀስ ሊቀንስ ይችላል። ይህም ዘግይቶ የሚደረግ የነርቭ መልሶ ግንባታ ውጤትን ሊገድብ ይችላል።
የጊዜ አስፈላጊነት
በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት: ሐኪሞች የጡንቻ ኃይልን፣ ስሜትን እና የነርቭ ተግባርን የማገገም ምልክት ለማየት ይከታተላሉ።
ከ3–6 ወራት አካባቢ: ነርቮቹ ጠቃሚ የማገገም ምልክት ካላሳዩ የነርቭ መልሶ ግንባታ ቀዶ ጥገና ሊታሰብ ይችላል።
በ1 ዓመት ውስጥ: ሕክምና ከዚህ ጊዜ በላይ እንዳይዘገይ በአጠቃላይ ይመከራል፤ ምክንያቱም ለረጅም ጊዜ የነርቭ ምልክት አለመኖር ጠቃሚ የጡንቻ ተግባርን የመመለስ እድል ሊቀንስ ይችላል።
በጊዜው በስፔሻሊስት መመርመር ነርቮቹ በተገቢው ሁኔታ እያገገሙ መሆናቸውን ወይም ቀዶ ጥገና በተገቢው ጊዜ መደረግ እንዳለበት ለማወቅ ይረዳል።
ከብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት በኋላ ማገገምን የሚወስኑ ሁኔታዎች
የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት ማገገም ለብዙ ወራት ወይም ከዚያም በላይ ሊወስድ ይችላል። የተጎዱ ነርቮች ወደ ሚቆጣጠሯቸው ጡንቻዎች እንደገና ማደግ ስለሚያስፈልጋቸው ሂደቱ ጊዜ ይወስዳል።
የማገገም ሁኔታን ሊጎዱ የሚችሉ ሁኔታዎች፦
የነርቭ ጉዳቱ ዓይነትና ክብደት
የጉዳቱ ቦታ
በጉዳቱና በሕክምናው መካከል ያለው ጊዜ
ነርቩ ወደ ተጎዳው ጡንቻ ለመድረስ እንደገና ማደግ የሚጠበቅበት ርቀት
አስፈላጊ ሲሆን የሚደረግ ቀዶ ጥገና
በተሀድሶ ሂደት የሚታይ እድገት
መደበኛ ክትትል በጡንቻ ኃይል፣ በስሜትና በጡንቻ ተግባር ላይ የሚኖሩ ለውጦችን ለመከታተል ይረዳል። ተሀድሶ/ ማገገሚያም (Rehabilitation) የመገጣጠሚያ እንቅስቃሴን ለመጠበቅ፣ መደንዘዝን ለመቀነስ እና ጠቃሚ የክንድ ተግባር እንዲመለስ ለመደገፍ ይረዳል።
በቬጃታኒ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል የብራኪያል ፕሌክሰስ ጉዳት (Brachial Plexus Injury) ሕክምና
በቬጃታኒ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል የኒውሮሳይንስ ማዕከል (Neuroscience Center) ስፔሻሊስቶች ውስብስብ የብራኪያል ፕሌክሰስ ጉዳቶችን በሚከተሉት ዘዴዎች ይገመግማሉ፦
የኒውሮሎጂ ምርመራ
የምስል ምርመራዎች
የነርቭ ተግባር ምርመራ
የአካል ተሀድሶ/ ማገገሚያ (Rehabilitation)
አስፈላጊ ሲሆን የቀዶ ጥገና ሕክምና
ዓላማው የጉዳቱን ሁኔታ በትክክል መለየት፣ ሕክምናውን በተገቢው ጊዜ ማቀድ እና ታካሚው የተጎዳውን ክንድ በተቻለ መጠን እንደገና እንዲጠቀም መርዳት ነው።
በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች (FAQ)
የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ምልክቶቹ በጉዳቱ ቦታና በክብደቱ ላይ ይመሰረታሉ። ታካሚዎች የክንድ ድካም፣ መደንዘዝ፣ መወጋገር፣ ህመም ወይም ትከሻን፣ ክንድን ወይም እጅን ለማንቀሳቀስ መቸገር ሊያጋጥማቸው ይችላል።
እንደ ክንድን ማንሳት ወይም እቃ መያዝ ያሉ የዕለት ተዕለት ተግባራትም ሊከብዱ ይችላሉ።
የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት በአዲስ ተወለዱ ሕፃናት ላይ ሊከሰት ይችላል?
አዎ። በወሊድ ወቅት የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት ሊፈጠር ይችላል፤ በተለይም የሕፃኑ ትከሻ በወሊድ ጊዜ ሲጣበቅ።
የነርቭ መዘርጋት የሕፃኑን የክንድ እንቅስቃሴና ስሜት ሊጎዳ ይችላል። ቀደም ብሎ መመርመር ሕፃኑ ክትትል፣ ተሀድሶ/ ማገገሚያ (Rehabilitation) ወይም ሌላ ሕክምና እንደሚያስፈልገው ለመወሰን ይረዳል።
ለብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት ምን ዓይነት ሕክምናዎች አሉ?
ሕክምናው በነርቭ ጉዳቱ ክብደት እና ነርቮቹ የማገገም ምልክት እያሳዩ መሆናቸው ላይ ይመሰረታል።
የሕክምና አማራጮች፦
በተመረጡ ሁኔታዎች የጅማት ወይም የጡንቻ ማስተላለፍ ሕክምና
ተሀድሶ/ ማገገሚያ (Rehabilitation) እና ቅርብ ክትትል
የነርቭ ጥገና (Nerve Repair)
የነርቭ ግራፍቲንግ (Nerve Grafting)
የነርቭ ማስተላለፍ (Nerve Transfer)
ከብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ጉዳት ማገገም ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?
የማገገሚያ ጊዜው በተለይም የነርቭ ጉዳቱ ከባድ ከሆነ ፤ ብዙ ወራት እና ከዚያም በላይ ሊወስድ ይችላል።
ማገገም በሚከተሉት ላይ ይመሰረታል፦
በተሀድሶ/ ማገገሚያ (Rehabilitation) ሂደት የሚታየው እድገት
የጉዳቱ ቦታ
የጉዳቱ ክብደት
ሕክምና በምን ያህል ፍጥነት እንደተጀመረ
ቀዶ ጥገና ያስፈለገ መሆኑ
በተሀድሶ/ ማገገሚያ (Rehabilitation) ሂደት የሚታየው እድገት
የብራኪያል ፕሌክሰስ (Brachial Plexus) ቀዶ ጥገና መቼ ሊያስፈልግ ይችላል?
ነርቩ ከተቀደደ ወይም ከአከርካሪ አጥንት ተነጥሎ ከወጣ ወይም የክንድ ተግባር ከጊዜ በኋላ በቂ መሻሻል ካላሳየ ቀዶ ጥገና ሊያስፈልግ ይችላል።
ውሳኔው እንዲሁም በሚከተሉት ላይ ይመሰረታል፦
የተጎዱት ነርቮች
የቀረው የእንቅስቃሴ መጠን
ከጉዳቱ ጀምሮ ያለፈው ጊዜ
ቀደም ብሎ መመርመር በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም የነርቭ መልሶ ግንባታ በተገቢው የጊዜ መስኮት ውስጥ ሲደረግ የተሻለ የማገገም እድል ሊኖረው ይችላል።
ለተጨማሪ መረጃ
የኒውሮሳይንስ ማዕከል (Neuroscience Center) ቬጃታኒ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል
ስልክ፦ (+66) 2-734-0000Ext. 5400
የአማርኛ ስልክ መስመር: (+66) 90-907-2560
Medically Reviewed by
DR. EKKAPOT JITPUN
Surgery
Neuroscience Surgery
Readers’ Rating
0.0 out of 5 stars (based on 0 reviews)