የጤና መረጃዎች

የጸረ ባክቴሪያ መድሃኒት አወሳሰድ መመሪያዎች

Share:

ብዙ ሰዎች የጸረ ባክቴሪያ መድኃኒቶች አጠቃቀም እና እነዚህ መድሃኒቶች ከጸረ ብግነት መድሃኒቶች ጋር ምን እንደሚለያያቸው ለማወቅ ግራ ሲጋቡ ይታያል፡፡በእነዚህ መድሃኒቶች የአጠቃቀም ክፍተት ካለ ለከፋ የጤና ችግር የመጋለጥ እድል ይኖራል፡፡ይህ ጽሁፍም የተዘጋጀው ይህንን ግራ መጋባት በተወሰነ መልኩ ለማስተካከል እንዲሁም በህብረተሰቡ ውስጥ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡

ጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች፡- እነዚህ የጸረ ባክቴሪያ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ መድሃኒቶቹም የሚታዘዙት በባክቴሪያ ምክኒያት የሚመጡ ኢንፌክሽኖችን ለማከም ብቻ ነው፡፡በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ የመድሃኒት ዝርዝሮችን ስንመለከት ፡-ፔኒሲሊን፤አምፒሲሊን፤አሞክሳሲሊን፤ኢሪትሮማይሲን፤ቴትራሳይክሊን፤ክሊንዳማይሲን እና ኖርፍሎክሳሲን የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡

ጸረ ብግነት መድሃኒቶች፡- በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ መድሃኒቶች ደግሞ የሰውነት ብግነት ምልክቶችን ለምሳሌ እንደ ህመም፤የሰውነት ሽፍታን፤እብጠት እና ትኩሳት የመሳሰሉትን የሚያስከትሉ ምን አልባትም ምንጫቸው ባክቴሪያ ያልሆነ ህመሞችን ለመቆጣጠር ነው፡፡በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ መድሃኒቶችን ዝርዝር ስንመለከት ደግሞ፡- ኢቦፕሮፊን፤ዳይክሎፌናክ እና አስፕሪን ይጠቀሳሉ፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች የሚያስፈልጉት በባክቴሪያ ምክኒያት የሚመጡ አንዳንድ ህመሞችን ለማከም ነው፡፡

ለምሳሌ፡-

  • የሳምባ ምች ህመም
  • የቲቢ በሽታ
  • የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን
  • በባክቴሪያ የሚመጣ የቶንሲል ህመም የመሳሰሉት ይገኙበታል

3ቱ የጸረ ባክቴሪያ መድሃኒት አወሳሰድ መመሪያዎች

  1. የታዘዘልዎትን መድሃኒት በሀኪሙ ትእዛዝ መሰረት ወስደው ይጨርሱ ይህም ማለት ከታዘዘው ያነሰ ወይም ደግሞ በራስዎ ፍቃድ ጨምረው አይውሰዱ
  2. መድሃኒትዎን በትክክለኛው ሰዓት መውሰድ እንዳለብዎት አይርሱ
  3. መድሃኒትዎን በሀኪም ለታዘዘልዎት ጊዜ ያህል ብቻ ይውሰዱ

እዚህ ጋር ማሳሰብ የምፈልገው ነገር ጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች ለባክቴሪያ መድሃኒትነት ብቻ እንጂ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጡ ህመሞችን ለማከም አይመረጡም፡፡ትክክለኛ ያልሆነ የፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች አጠቃቀም በአሁኑ ሰዓት አሳሳቢ የህብረተሰብ ጤና ጠንቅ ለሆነው ሰውነት የጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶችን መላመድ ችግር ሊያጋልጠን ይችላል፡፡

ሰውነት የጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች መለማመድ ተፈጠረ የምንለው ባክቴሪያዎቹ የዚህን መድሃኒት አሰራር በማቆም ወይም በሌላ መንገድ የመድሃኒቱን ውጤታማነት ሲቀንሱ ነው፡፡በዚህም ምክኒያት ባክቴሪያው እያደገ፤እየጠነከረ እንዲሁም ለማከም አስቸጋሪ የሚሆንበት ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡

በአጠቃላይ ይህ ችግር እንዳይከሰት ለመከላከል ወይም ለመቀነስ ማንኛውንም አይነት መድሃኒት ከመውሰዳችን በፊት ለሀኪም ማማከር አስፈላጊ ነው ፡፡ለምሳሌ፡-መጠነኛ ትኩሳት፤ሳል፤የአፍንጫ ማፈን ወይም የጉንፋን ስሜት ካለዎት በቂ ውሃ መጠጣት እንዲሁም እረፍት ማድረግ መድኃኒት መውሰድ ሳያስፈልግ የህመም ስሜቱ እንዲጠፋ በቤታችን ማድረግ የምንችላቸው ቀላል እርምጃዎች ናቸው፡፡