የጤና መረጃዎች

የመጀመሪያ የጡት ካንሰር ሕክምና

Share:

ከCOVID-19 በተጨማሪ የካንሰር በሽታ ሕክምናው መዘግየት እንደሌለበት ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡ ለጡት ካንሰር የሚሰጡ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምናዎችን እንይ፦

የጡት ካንሰር ሴቶችን ከሚያጠቁ በጣም የተለመዱ የካንሰር አይነቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የጡት ካንሰር እንደሌሎች የካንሰር ዓይነቶች በክብደት ደረጃው ሲለካ 4 ደረጃዎች አሉት፡፡ ከደረጃ 1-3 ያለ ካንሰር ማለት በመጀመሪያወች ደረጃ ያለ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ያልተሰራጨና መታከም የሚችል የካንሰር ደረጃ ነው፡፡ ደረጃ 4 የምንለው ደግሞ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የተሰራጨ ካንሰር ማለት ነው፡፡

የጡት ካንሰር ሕክምና መርሆዎች ሦስት ጠቃሚ ክፍሎች አሉት እነሱም፦

1. ቀዶ ጥገና፦ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 3 ላሉ የጡት ካንሰር ዓይነቶች ቀዶ ጥገና ዋና ሕክምና ዘዴ ነው ፣ እንዲሁም ለተወሰኑ ደረጃ 4 ላይ ለደረሱ ኬዞችም ቀዶ ጥገና የህክምና ምርጫ ይሆናል። ሁለት ዓይነት የቀዶ ጥገና ዓይነቶች አሉ እነሱም፦ ካንሰር ያለበትን ቦታ ብቻ ለይቶ የማስወገድ ቀዶ ጥገና (Breast conservation surgery) እና በካንሰር የተጠቃውን ጡት ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ቀዶ ጥገና (Mastectomy) ይባላሉ።

2. ሲስተሚክ ትሪትመንት (Systemic Treatment)፦ የካንሰር ሕዋሳት ለማከም በመላው ሰውነት ውስጥ የሚሰራጩ መድኃኒቶች ማለትም ኬሞቴራፒ፣ ሆርሞናል ቴራፒ እና ታርጌትድ ቴራፒ (HER2) በመጠቀም የሚደረግ ህክምና ነው፡፡

  • ኬሞቴራፒ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ላይ ያለ የጡት ካንሰርን ለማከምና ካንሰሩ ተመልሶ እንዳይመጣ ለመከላከል ያገለግላል፡፡ ነገር ግን ደረጃ 4 ላይ ለደረሰ ካንሰር ኬሞቴራፒ የህመሙን ስቃይ ለመቆጣጠርና የበሽተኛውን እድሜ ለማራዘም ያገለግላል።
  • የሆርሞናል ቴራፒ በዋነኝነት በአፍ የሚወሰድ (የሚዋጥ) መድሃኒት ነው፡፡ ሆርሞናል ቴራፒ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ያለ የጡት ካንሰርን ለማከም ያገለግላል። የዕጢው እድገት ከሆርሞኖች ጋር የተያያዘ እና ሆርሞኖች እጢውን የሚመግቡት ከሆነ ካንሰሩ ተመልሶ እንዳይመጣ ሆርሞናል ቴራፒ እንዲወሰድ ይደረጋል። እንዲሁም ደረጃ 4 ላይ ለደረሰ ካንሰርም የሕክምና አማራጭ ነው፡፡
  • ታርጌትድ ቴራፒ ወይም የጡት ካንሰር እንዲፈጠር የሚያደርገው የዘረመል አይነት (HER2) ላይ ያነጣጠረ መድሃኒት፦ ይህ መድሃኒት ከተለመደው ከፍ ያለ የHER2 ዘረመል ቁጥር ለተገኘባቸው የጡት ካንሰር ህመምተኞች በሽታው ተመልሶ እንዳይመጣ ለመከላከል እንዲወሰድ ይደረጋል። እንዲሁም ደረጃ 4 ለደረሰ ካንሰር የህክምናውን ውጤታማነት ከፍ ለማድረግ ከኬሞቴራፒ ጋር በጋር በመሆን አማራጭ የህክምና ዘዴ ነው፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት የሕክምና አማራጮች በተጨማሪ የጡት ካንሰርን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከም የሚችሉ ሌሎች አዳዲስ መድኃኒቶችም አሉ፡፡

3. የጨረር ህክምና (Radiotherapy)፦ የጨረር ህክምና ከቀዶ ጥገናው በኋላ ካንሰሩ ተመልሶ
እንዳይመጣ እንዲሁም የተሻሉ ውጤቶችን ለማግኘት የካንሰር ሕዋሶችን ለመግደል ከፍተኛ መጠን ያለውጨረር በመጠቀም የሚከናወን ሕክምና ነው ፡፡ ለማጠቃለል ያህል የሚሰጠው ሕክምና በካንሰሩ ዓይነት ፣ ካንሰሩ በደረሰበት ደረጃ እንዲሁም በሽተኛው ያለበት አካላዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው ፡፡

  • Readers Rating
  • Rated 3.7 stars
    3.7 / 5 (5 )
  • Your Rating
Related Posts